የ2006ዓ.ም የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

6

በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 የሚከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን መሪነት ከ13 ታቦታት በላይ በሚያድሩበት በጃን ሜዳ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ  ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡ የዓመቱ ተረኛ የሆነው የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ ‹‹ ተሰሃልከ እግዚኦ ምደረከ ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ እም ሰማያት ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም››በማለት ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል፡፡የደብሩ ፍቁረ እግዚእ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትም “በሰላም አስተርአየ፡ አስተርአየ ወልደ አምላክ፤ ወተወልደ በሀገረ ዳዊት ተወልደ፤ በዮርዳኖስ ተጠምቀ ከመይቤዝወነ” እያሉ ዝማሬ በማቅረብ በዓሉን አድምቀውታል::

 በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ዐበይት በዓላት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ይህም በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ፤ በማእከለ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ከዋዜማው ከጥር 10 ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ፤ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን መሠረት በማረድግ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ታቦታት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ በካህናትና ዲያቆናት፤ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ፤እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራንና ምዕመናን በዝማሬ በመታጀብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ታቦት ማደሪያ በማምራት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሔድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ማምራቱን ያበስራሉ፡፡ ‹‹ያን ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ ዮሐንስም በዮርዳኖሰ ወንዝ አጠመቀው›› እንዲል፡፡/ማቴ.3፡1/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስራቿን መድኅነ ዓለም ክርስቶስን ለዓለም የምትሰብክበት፣ ከእርሱም ያገኘችውን፣ ይህም ዓለም እንደሚሰጠው ያልሆነውን፣ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ትሕትና ለዓለሙ ትሰብክበታለች፡፡ እንዲሁም ለሀገራችን በጎ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ተደንቀው የሚያዩትና በመስተንግዶው የሚደመሙበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ በዓሉን በልዩ ትኩረት ታከብራለች፡፡

e1

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ከ46 ያላነሱ የታቦታት ማደሪያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል :-የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፣ የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ የገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም፣ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ቅዱሳን ማርያም፣ የደብረ ነጐድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ የቀበና መካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ፣ የገነተ ኢየሱስ፣ የአንቀፀ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ታቦታት የዓለምን ትኩረት በሚስበው በጃን ሜዳ ያደሩ ሲሆን ታቦታቱ ከየመንበረ ክብራቸው ተነስተው ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሀገር ውጭ እና ከሀገር ውስጥ የመጡ ጐብኚዎች፣ በርካታ ካህናት እና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እና ማህበረ ምዕመናን ከቦታው የተገኙ ሲሆን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና በሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ያሬዳዊ ወረቦች ቀርበዋል፡፡
በብፁዕ አቡነ ሰላማ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል እና በዓታ ለማርያም ገዳማት የበላይ ጠባቂ አጭር ትምህርት ተሰጥቶአል ብፁዕነታቸው በሰጡት ትምህርት ይህ ዕለት አባታችን አዳም እና እናታችን ሄዋን ከወደቁበት ቦታ የተነሱበት ዕለት ነው፡፡ ነቢያት ፈኑ እዴከ በማለት ልመና ሲአቀርቡ ኑረዋል ዓመተ ምህርት የታየው በዛሬው ዕለት ነው፡፡ ጌታ በመወለዱ ሰውና መላእክት፣ ህዝብ እና አህዛብ ነፍስና ሥጋ አንድ ሆነዋል፡፡ ዕርቅ ተመሥርቷል አዳም እና ሔዋን ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ወጥተዋል ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ በዮርዳኖስ የተጣለው የዕዳ ደብዳቤአችን ተደምስሶልናል፡፡ እኛም ከአብርከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ተወልደናል አስቀድሞ በነቢዩ ሕዝቅኤል በጥሩ ውሀ እረጫችሁአለሁ እናንተም ትነፀላችሁ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ ፍጡሩ ዮሐንስ ጌታን ሲአጠምቀው በማን ስም አጠምቅሀለሁ የሚል ጥያቄ ጠይቆት ስለነበር ጌታም ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለኒ በል በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ ትምህርት ካስተማሩ በኋላ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚከተለውን ትምህርታዊ መልእክትና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ዓመቱን ሁሉ በሰላም ጠብቆ ላገናኘን ለአምላካችን ለአግዚአብሔር ክብር እና ምሥጋና ይግባሉ አሜን መጽአ ኢየሱስ እምገሊላ ከመይጠመቅ እም ዮሐንስ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የተጫነብንን ሸክም አስወግዶልናል፡፡ ከዲያብሎስ ቁራኛነት አላቀቀን የመንግሥቱ ዜጐች አደረገን፡፡ የመንግሥቱ ዜጐችም የሆንበት በጥምቀት ነው፡፡ ለዚህ ታላቅ በዓል ያደረሰን አምላካችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን በማለት ቅዱስነታቸው አጠር ያለ መልእክት አስተላልፈው ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ በማግሥቱ ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም ከጧቱ አንድ ሰዐት ሲሆን ልብሰ ተካህኖ በለበሱ ካህናተ ጸሎተ ወንጌል ተደርሷል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ኪዳን ካደረሱ በኋላ ቅዱስነታቸው ጥምቀተ ባህሩን ባርከው በርካታ ምዕመናንን የበረከት ጸበል እንዲረጩ ተደርጓል በማያያዝ በመዘምራን እና በሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተዘጋጁ መጽሔቶች እና በራሪ ጹሑፎች ለብፁዓን አባቶች፣ ለክብር ዕንግዶች እና ለምዕመናን በነፃ ተሠራጭቷል፡፡
ከዚያም በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ዶ/ር ዮሊየስ ሊቀ ጳጳስ የህንድ ኦርቶዶክስ ተዋሖዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል የሚከተለውን መልአክት አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ የተሰበሰባችሁ ታላቅ ሕዝብ በቅድሚያ በሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በፓትርያርኩ ስም ለዚህ ለተቀደሰ ጉባኤ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡
የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ ግንኙታችንንም የበለጠ አጠናክረን እንቀጥላለን በዚህ ቅዱስ በዓል እና በዚህ ታላቅ ሕዝብ በመካከል በመገኘቴ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ይህንን በዓል ስናስብ የስላሴን አንድነት እና ሶስትነት እናያለን በዮርዳኖስ በጥምቀት ኃጢአታችን ተወግዷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የእውነት ምስክር ነው፡፡ ሁላችንም እውነተኞች ልንሆን ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ ነው ቤተ ክርስቲያንም የነቢይነት ሥራ ትሠራለች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታን በማጥመቁ ምንኛ እድለኛ ነው የቅዱስ ዮሐንስ ክህነት የቤተ ክርስቲያናችንን ማዕረገ ክህነት ታላቅነት ያሳያል፡፡
ለብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ዕድሜ እና ጤንነትን እመኛለሁ በዚህ ታላቅ ሕዝብ መካከል በመገኘቴ የተሰማኝን ደስታ እየገለፅኩኝ ንግግሬን አቆማለሁ አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ብለዋል ከዚህ በመቀጠልም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከንቲባን በመወከል ከበዓሉ ላይ የተገኙት ክቡር አቶ ኤፍሬም ግዛው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የሚከተለውን ንግግር አድርገዋል፡፡
ቅዱስ አባታችን የተከበራችሁ የሃይማኖት መሪዎች፣ በዚህ በዓል ላይ የተገኛችሁ የክብር እንግዶች እንኳን ለዚህ ታላቅ በዓል አደረሳችሁ በህገ መንግሥታችን እንደተደነገገው በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል መብት አላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሁሉም ሃይማኖቶች ክብር በመስጠት ተከባብሮ እና ተቻችሎ እንደሚኖር እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ አንዳን ቦታዎች ጽንፈኝነት እና አክራሪነት የዓለም ተምሳሌት የሆነውን የመከባበር ባህላችንን በመጋፋት የሚአሳዩት ጉዳይ ይታያል፡፡
ሆኖም ሕዝባችን በመቻቻልና በመከባበር ጉዳዩንም በጥንቃቄ በመያዝ በሰላም እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ሲአደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም የሃይማኖት አባቶች ለዘመናት የነበረውን ተቻችሎ የመኖር ባህል እንዲቀጥል ለማድረግ የራሳቸውን ሚና እና ድርሻ ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ አሁን በሀገራችን ከፍተኛ የልማት እድገት እያሳየን ባለንበት ሁኔታ ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚሞክሩትን የለውጥ አደናቃፊዎችን በመከላከል የጀመርነውን የልማት ዕድገት ጠንክረን እንድንወጣ ጥሪአችንን እያስተላለፍን በዓሉ የደመቀ እንዲሆን እንመኛለን፡፡ አመሰግናለሁ ብለዋል በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚከተለውን አባታዊ መመሪያና ትምህርታዊ መልእከት አስተላልፈዋል፡፡
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያት ልትሰጥ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ መጣ፡፡ መንግሥተ ሰማያት የምትወረሰው በእምነት ስለሆነ ንስሐ ግቡ አለ፡፡ የእግዚአብሔርንም መንገድ ጥረጉ ጐባጣው ይቅና፣ ተራራው ዝቅ ይበል ጐድጓዳው ይሙላ እያለ ሰበከ፡፡
በድሮ ዘመን መኪናም ሆነ አይሮፕላን አልነበረም ነገሥታቱ መኳንቱ የሚጓዙት በፈረስ እና በበቅሎ ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያት አባጣ ጐርባጣውን መሬት በቁፋሮ እንዲስተካከል ከነገሥታቱ ትእዛዝ ይተላለፍ ነበር፡፡ ዮሐንስም የተናገረው ይህንኑ ነበር አባጣ ጐርባጣው ይስተካከል ሲባል ልባችሁን አንፁ ማለት ነው፡፡ የልባችንን አበባ ጐርባጣ እንድናስተካክል ነው መጥምቁ ዮሐንስ የተናገረው በኃጢአት የተበላሸውን ልባችንን ልናነፃ ይገባናል በሃይማኖት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንችላለን የልባችንን መንገድ ለእግዚአብሔር ልናስተካክልለት ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ወደ ልባችን እንዲገባልን ተንኮልና ክፋትን ልናስወግድ ይገባናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደልባችን እንዲገባ የልባችንን መንገድ እናስተካክል ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ እኩል ነው በአርአያ ሥላሴ ተፈጥሮአልና፡፡
ልባችን መራራቅ የለበትም ሰው ድሀ ሀብታም እየተባባለ ሊራራቅ አይገባም ተራራው ዝቅ ይበል የተባለውም ይህንን ነው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ክቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በዚህ ዓለም ተመላልሷል፡፡ የመንግሥተ ሰማይንም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የወንጌል ቃል በራስህ ሊደረግብህ የማትወደውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ ብሏል፡፡ እኛ እንድንጨቆን፣ እንድንራብ፣ እንድንጠማ፣ እንድንታረዝ፣ የማንፈልግ ከሆነ ለወንድሞቻችን ለእህቶቻችን ልናስብላቸው ይገባናል፡፡ በኃጢአት እና በጣኦት የተበላሸውን ልባችንን ልናነፃው ያስፈልጋል በዛሬው ዕለት ጌታ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀው የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት በደላችንን ሊአስወግድልን ነው እንጂ እርሱ በደል፣ ነውር ኑሮበት አይደለም፡፡ በኃጢአት ምክንያት ሰው ከእግዚአብሔር ተለይቶ እንዲኖር እና መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ታውጆበት ነበር፡፡ አሁን ግን ያ መርገም ተወግዷል ስለዚህ ሰውነታችንን ልናስተካክል ይገባናል፡፡
በሀገራችን የሚካሄደው ልማት እና ብልፅግና ግቡን እንዲመታ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት፡፡ የሀገር ልማት የወገን ልማት ነው በሀገራችን ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን ልናደርግ ይገባናል የሰፈነውን ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን ልናደርግ ይገባናል፡፡ የሰፈነውን ሰላምና ፍቅር ለማወክ የሚነሳሱት ሁሉ ሰላማችንን እና ጸጥታችንን ለማደፍረስ የሚሞክሩ መቆጠብ አለባቸው፡፡ ለሀገር የሚጠቅመው ሰላም፣ ህብረት ብልፅግና ነው፡፡ ይህ እንዲጸና ነቅተን እና ተግተን መጠበቅ አለብን የቤተ ክርስቲያን መልእክት ይህ ነው፡፡ ይህንን መልእክት ሁሉም እንዲአስተላልፈው ያስፈልጋል፡፡
ሁሉም መተባበር አለበት ሁከት ፈጽሞ መኖር የለበትም፡፡ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የብልፅግና በዓል ይሁንላችሁ እግዚብሔር ይባርካችሁ በማለት ቅዱስነታቸው የጥምቀተ ባህሩን የጧት መርሐ ግብር በጸሎትና በቡራኬ አጠናቅቀዋል፡፡

{flike}{plusone}