ለቅዱሳን ፓትርያርኮችና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው

i03

ከአጸደ ሥጋ ዓለም በሞት ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው፡፡  ጸሎተ ፍትሐቱ በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣እንዲሁም ለብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ነው፡፡
 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “አባቶቻችን ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን አደራ ጠብቀው በሚችሉት አቅም ሊሠሩት የሚገባውን ሁሉ ሠርተው አልፈዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀውና ሃይማኖትን አጽንተው በማቆየት ለእኛ አስተላልፈዋል” ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም “እናትና አባትህን አክብር የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በዚህ ቦታ ተገኝተናል በመንፈስ ወልደውና በምግባር አሳድገው ለዚህ ስላበቁን እነሱን ማክበርና ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ የሚመሰገን ነው፡፡” በማለት ቀደምት የቤተክርስቲያን አበውን መዘከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ “ሰው በዚህ ዓለም ይሞታል፤ የማይሞተው ግን የሠራው ሥራ ነው፤ ለሰው ሐውልቱ ሥራው ነው ስለሆነም ዛሬ የዘከርናቸው እንደነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለ ሃይማኖትና ጳውሎስ ስማቸው ሕያው ነው፡፡ ብለዋል፡፡
በዚሁ እለት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱ የተሠራው በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሆን፤ ወጭውን ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሸፈኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡
ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ስለ ሐውልቱ መሠራት ሲገልጹ “የቅዱስ አባታችን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐውልት በዚህ ቦታ የተተከለው ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በመላው ኢትዮጵያ የሠሩት ሥራ ነው፡፡
በዚህም ዘለዓለም ሲታሰብ ይኖራል፡፡ ሰው በታላቅነቱና በሠራው ሥራ ሲታወስ ይኖራል፤ እኒህ ታላቅ አባትም በዚህ ስፍራ የቆመው ሐውልት ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሔዱበት ቦታ ሁሉ የሠሩት ሥራ ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡

በዕለቱ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት  ጸሎተ ፍትሐትና የመታሰቢያ ሐውልት ምርቃት መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

{flike}{plusone}