ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2007 ዓ.ም.የልደት በዓልን አስመልከቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደት ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን!!
– በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
– ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
– የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
– በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
– እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ፣ ስሙም ድንቅ መካርና ኃያል አምላክ የሆነው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ሰባት ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!
‹‹ወውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ፤ ያ ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛ ላይም አደረ›› (ዮሐ. 1፣14)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ስናከብር ከሁሉ በፊት የእርሱን ማንነት በማውሳት፣ በመረዳትና የእምነት ግብረ መልስን በመስጠት ልናከብር እንደሚገባ መገንዘቡ ተገቢ ነው፤
ከዚህ አኳያ ለመሆኑ የተወለደው ማን ነው? ለምንስ ተወለደ? በልደቱ ዕለት ለዓለም የተላለፈው አጠቃላይ መልእክትስ ምንድን ነው? የሚለውን ማየት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፤
ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደሚያስተምሩን ከሦስቱ አካላተ እግዚአብሔር አንዱ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ስለሆነ በተለየ ኩነቱ ቃል፣ ቃለ አብ፣ ቃለ እግዚአብሔር፣ አካላዊ ቃል ተብሎ ይጠራል፤ (መዝ. 32፣6፤ ዮሐ. 1፣1-2፤ ራእ. 19፣13)
ቃል ከልብ እንደሚገኝ አካላዊ ቃልም ከአብ የተገኘ ነው፤ ይሁንና ቃል ከልብ በመገኘቱ ደኃራዊ አይባልም፤ ልብም ቃልን በማስገኘቱ ይቀድማል አይባልም፣
በተመሳሳይም አካላዊ ቃል ከአብ በመገኘቱ ደኃራዊ አይባልም፣ የአካላዊ ቃል አስገኝ የሆነው አብም አስገኝ በመሆኑ ከወልድ ይቀድማል አይባልም፡፡
በህልውናም (በአኗኗር) ከቃል የተለየ ወይም የቀደመ ልብ እንደማይኖር ሁሉ፣ ከአካላዊ ቃል የተለየ ወይም የቀደመ የአብ ህልውና (አኗኗር) የለም፤
ቃል የሚለው ስም እኩል የሆኑ የሦስቱ አካላተ እግዚአብሔር ቅድምና እና ህልውና በምሥጢር ያገናዘበና በትክክል የሚገልጽ በመሆኑ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመለኮታዊና በቀዳማዊ ስሙ ቃል ብሎታል፤
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤
ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም›› በማለት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት በማያሻማ መልኩ ያረጋግጣል፤ (ዮሐ. 1፣1-3)፡፡
እግዚአብሔር አብ አካላዊ በሆነ ቃሉ በእግዚአብሔር ወልድ ፍጥረታትን ሁሉ እንደፈጠረ፣ አካላዊ በሆነ እስትንፋሱ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ለሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ሕይወትን እንደሰጠ በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ በግልጽ ተቀምጦአል፤ (ዘፍ. 1፣1-3፤ መዝ. 32፣6፤ ዘፍ. 2፣7፤ ሮሜ 8፣11)፡፡
በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ሥጋችንን በመዋሐድ ሰው ሆኖ ተወለደ እየተባለ ያለው ፍጥረታትን በሙ ሉ የፈጠረ፣ ከተፈጠረው ፍጥረት አንዳች ስንኳ ያለእርሱ የተፈጠረ ምንም እንደሌለ የተነገረለት አካላዊ ቃል ማለትም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ነው፤
አካላዊ ቃል ከዘመን መቆጠር በፊት በመለኮታዊ ርቀትና ምልአት ከፍጡራን አእምሮ በላይ በሆነ ዕሪና፣ ዋሕድና፣ ቅድምና፣ ኩነትና ህልውና እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ የነበረ ሲሆን በሞቱ የእኛን ዕዳ ኃጢአት ተቀብሎ ከሞተ ኃጢአት ሊያድነን በአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም መጋቢት 29 ቀን መዋች የሆነው ሥጋችንን በማኅፀነ ማርያም ተዋሕዶ ሥጋ ሆነ፤ (ዮሐ. 1፣14)፡፡
ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲሆነው ታሕሣሥ 29 ቀን እንደ ትንቢቱ ቃል በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ተወለደ፤ የምሥራቹም ‹‹ዛሬ መድኅን ክርስቶስ ተወልዶላችኋል›› ተብሎ በመላእክት አንደበት ተበሠረ፤ (ሉቃ. 2፣10-12፤ ማቴ. 2፣1-11)፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ በተወለደ ጊዜ በቃል ርስትነት ሰው እግዚአብሔር ሆነ፤ በሥጋ ርስትነት አካላዊ ቃል ሰው ሆነ፤ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ይህንን ተዋሕዶ የተመለከቱ የሰማይ ሠራዊትም አካለ ሰብእን በተዋሕዶተ ቃል ለአምላካዊ ክብር ላበቃ ለእርሱ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ይሁን፤ በጎ ፈቃዱም ለሰው ይሁን›› ብለው በደስታ ዘመሩ (ሉቃ. 2፣13-15)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያደረገው በጎ ፈቃድ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ላሉ ፍጥረታት ለማንም ያልተደረገ ነው፤ (ዕብ. 1፣1-14)፡፡
ምንም እንኳ ፍጥረታትን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብና የሚጠብቅ እርሱ ብቻ መሆኑ ቢታወቅም፣ አካሉን አካል አድርጎ በተዋሕዶ ወደአምላክነት ደረጃ ከፍ ያደረገው፣ በመንበረ መለኮት ያስቀመጠውና የሰማይና የምድር ገዢ ያደረገው ግን ከሰው በቀር ከፍጡር ወገን ሌላ ማንም የለም፤ (መዝ. 8፣4-6፤ ዕብ. 2፣16፤ ኢሳ. 9፣6-7)፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በተለየ ሁኔታ በስሟ ላይ ‹‹ተዋሕዶ›› የሚለውን ቃል መጠቀሟ የድኅነታችን መሠረት የቃልና የሥጋ ተዋሕዶ መሆኑን ለማሳየት ነው፤
ምክንያቱም ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ አይሞትምና፤ ቃል በሥጋ ካልሞተ ደግሞ እኛ ከሞትና ከኃጢአት ዕዳ ነጻ መሆን አንችልምና ነው፤
የአምላክ ሰው ሆኖ መወለድ ለሰው ልጅ ያስገኘለት ክብር እስከዚህ ድረስ መሆኑን መገንዘብና ማወቅ ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ነው፤
ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋችን ዛሬ በመለኮት ዙፋን ተቀምጦ ዓለምን ማለትም ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን በአጠቃላይ እየገዛ ይገኛል፤ (ዕብ. 2፣5-8)፡፡
ይህ ታላቅና ግሩም ምሥጢር የተከናወነው በሰው ብልሃትና ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ የተፈጸመ አስደናቂ ጸጋ ነው፤
በዚህ ፍጹም የተዋሕዶ ፍቅር ሰማያውያኑና ምድራውያኑ እውነተኛውን ሰላም ማለትም በጌታችን ልደት የአምላክና የሰው ውሕደት እውን ሆኖ ስላዩ ‹‹ሰላም በምድር ሆነ›› አሉ ፡፡
ሰማያውያኑ ፍጡራን ዛሬም ያለ ማቋረጥ ሰው ለሆነ አምላክ ይህንን የሰላም መዝሙር ይዘምራሉ፤ እኛ ምድራውያኑም የዘወትር መዝሙራችን ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚለው ሊሆን ይገባል፤
ምክንያቱም በሰላም ውስጥ ሃይማኖትን መስበክና ማስፋፋት አለ፤ በሰላም ውስጥ ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና አለ፤ በሰላም ውስጥ መቻቻል፣ መከባበርና መተማመን አለ፤ በሰላም ውስጥ መደማመጥና መግባባት አለ፡፡
ስለሆነም በልደተ ክርስቶስ ከተዘመረው መዝሙር የሰማነው ዓቢይ መልእክት ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚለው ነውና ከሁሉ በላይ ለእርስ በርስ መፋቀርና ለሰላም መጠበቅ ቅድሚያ መስጠት የዘወትር ግዳጃችን ሊሆን ይገባል፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱን ያደረገው በትሑታኑ መኖሪያ ማለትም በእንስሳቱ በረትና በእረኞቹ ሠፈር እንደነበር ልናስታውስ ይገባል (ሉቃ. 2፡6)
ይህንን ያደረገበት ዓቢይ ምክንያት በእርሱ ዘንድ የተናቀና ዝቅተኛ ነው ተብሎ የሚተው ፍጡር እንደሌለ ለማስተማር ነው (ማቴ. 10፡29-31)
ስለሆነም የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሆን እኛም ከልደቱ መልእክት ትምህርትን ወስደን በዚህ ቀን በጤና፣ በዕውቀት፣ በሀብትና በልዩ ልዩ ምክንያት አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ቁሳዊ ድህነት ከተጫናቸው ወገኖች ጋር አብረን በመዋል፣ አብረን በመመገብና እነርሱን ዘመድ በማድረግ በዓሉን ልናከብር ይገባል፤ (ማቴ. 25፡40)፡፡
በመጨረሻም፤
ልደተ ክርስቶስ መለያየትንና ጥላቻን ያስወገደ፤ በምትኩ እግዚአብሔርንና ሰውን በማዋሐድ ለሰው ልጅ አዲስ የድኅነት ምዕራፍን የከፈተ እንደሆነ ሁሉ፣ እኛ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያትም ድህነትን በአጠቃላይ ለመቀነስ የጀመርነው አዲስ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብር ከግብ ለማድረስ አሁንም ሌት ተቀን ጠንክረን በመሥራት ሀገራችንን በልማት እንድናሳድግ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታሕሣሥ 29 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
{flike}{plusone}