የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል G+3 ዘመናዊ ሁለገብ ሕንፃ አስመረቀ!!!
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያስገነባው ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ በመጠናቀቁ እሁድ ጥር 8/2008 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳት ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ሁለገብ ሕንፃው ተመርቋል ፡፡
በካቴድራሉ የቀረበው አጭር የሥራ ሪፖረት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“አቀድም አእኵቶቶ ለእግዚአብሔር” ሮሜ ፩፥፰
በእግዚአብሔር ፈቃድና ቸርነት ሥራው ሁሉ ተከናውኖ በዛሬዋ ዕለት ለካቴድራሉ ሁለገብ ሕንፃ ምረቃ በዓል በመብቃታችን በቅድሚያ ለልዑለ ባሕርይ አምላካችን ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያስገነባው ሁለገብ ሕንፃ በዛሬው ዕለት ለምረቃ ያበቃ መሆኑን እና በቀጣይም እያከናወነ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በተመለከተ አጠር ያለ መግለጫ እንዳቀርብ ቅዱስነትዎ እንዲፈቅዱልኝ ከፍ ባለ አክብሮትና ትሕትና እጠይቃለሁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ሆይ!
ይህ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ታላቅ ካቴድራል በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ተመሥርቶ በአገልግሎት ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ ከመዳበኛው መንፈሳዊ ተግባርና አገልግሎት ጎን ለጎን በልማት እንቅስቃሴውም ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ካቴድራል መሆኑን ሁላችንም ምስክርነታችንን የምንሰጥበት ሀቅ ከመሆኑም በላይ በእጃችን ዳሰን በዓይናችን ዓይተን የምናረጋግጠው ጉዳይ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ግርማዊነታቸው የካቴድራሉን ቤተ ክርስቲያን በሠሩበት ወቅት የመተዳደሪያውንም ጉዳይ ቀድመው በማሰባቸው በከተማ የተለያዩ ሕንፃዎች ከከተማ ውጪ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ መቶ ጋሻ መሬት በላይ መተዳደሪያ ሠርተውለት የነበረ ቢሆንም በአምባ ገነናዊው የደርግ ሥርዓተ መንግሥት የከተማ ትርፍ ቦታና በገጠሩም መሬት ላራሹ በሚል ሰበብ በዓዋጅ 47/67 በከተማም በገጠርም ያለው ይዞታ የተወረሰበት በመሆኑ ይዞታውን ሁሉ ሊያጣ ችሏል፡፡
ሆኖም በከተማ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች በኢፌዲሪ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያቱ እንደተመለሱ የሚታወስ ነው፡፡ ካቴድራሉ ግን በልማት እንቅስቃሴው ግንባር ቀደም እንደመሆኑ መጠንና በኋላም በቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዓዋዲ መሠረት ከተለያዩ እደ ጥበባት ጀምሮ ልዩ ልዩ ተቋማትን በማስፋፋት ለሌላው ምሳሌ ሆኖ ተገኘ እንጂ ራሱን የጣለበት ጊዜ የለም፡፡
በዚህም መሠረት ሕልውናው ሊጠፋ የነበረውን የካቴድራሉን ዘመናዊ ትምህርት ቤት የገጠሙትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ሁኔታው የጠየቀውን መሥዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡ ማለትም ከአጸደ ሕፃናት እስከ መሰናዶ ት/ቤት በማድረስ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ከቤተ ክርስቲያኒቱም ባለፈ በሐገር እና በዓለም ዙሪያ አንቱ የተባሉ ምሁራንን በማብቃት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚያም በተያያዘ መልኩ በካቴድራሉ ዙሪያ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ሕንፃዎችን በማስገንባት በልማት ሥራው እንቅስቃሴ ገቢ በመፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረገ ያለ መሆኑ በተጨባጭ የሚታይ ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን !
ክቡራን ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች!
በዚህ ታላቅ ካቴድራል እየተከናወኑ ያሉት የልማት ሥራዎች ሰፊ ይዘት ያላቸው ቢሆንም የግንባታ ሥራው ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በቅዱስነትዎ ቡራኬ ለምረቃ የበቃውን ሁለገብ ሕንፃ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ በጋራ በመሆን ሴቪየር አማካሪና ተቆጣጣሪ በመባል የሚታወቀውን አማካሪ ድርጅት የመጀመሪያ ፕላኑን በነፃ ያለምንም ክፍያ ሠርቶ ያቀረበልንን የመጀመሪያ ፕላን መሠረት በማድረግ የካቴድራሉ ቴክኒክ ክፍልም በአማካሪ ድርጅቱ ተሠርቶ የቀረበውን ፕላን ካየ በኋላ የጨረታ ሰነድ አዘጋጅቶ ሕጋዊ ጨረታ በማውጣት እና የተለያዩ ተቋራጭ ድርጅቶችን አወዳድሮ ለአሸናፊው ኤቢኤም ኮንስትራክሽን ለተባለው ድርጅት በመስጠት ከጥር ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ሕንፃ ግንባታው ሲካሄድ ከቆየ በኋላ በሥላሴ ፈቃድ እነሆ በዚህ ታሪካዊ ዕለት በቅዱስነትዎ ቡራኬ ተመርቆ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቶ ይገኛል፡፡
ይህም የካቴድራሉን ደረጃ በጠበቀ መልኩ በተገቢው አማካሪ ድርጅት (ኮንሰልታንሲ) እና የሕንፃ ተቋራጭ እንዲሁም ደግሞ በካቴድራሉ ልማት ኮሚቴ የቴክኒክ -ኮሚቴ የዕለት ተዕለት ክትትል እየተደረገ የሕንፃ ግንባታው ሥራ በተፈለገው ደረጃና ጥራት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
በመሆኑም የሥራ ጊዜያትን በባረከልን ቸሩ አምላካችን፣ በቅዱስነትዎ ብልህ አመራር ሰጪነትና ጸሎት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሌሎችም ድጋፍና ትብብር በባለቤትነት ሥራውን የሚመራው የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ክትትልና ትጋት በካቴድራሉ ዕቅድና ልማት ክፍል ከፍተኛ ጥረት በመላው ማኅበረ ካህናትና ሠራተኞች ትብብር ከዚህ ካማረ ውጤት ላይ ሊደርስ በቅቷል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ክቡራን ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች!
ከዚሁ ጋር በማያያዝም የሕንፃውን አጠቃላይ ወጪና ይዘት አጠር አድርገን ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡
ጠቅላላ የሕንፃው ግንባታ ወጪ
1.ለሕንፃ ተቋራጩ ብር ከ 18‚000‚000 በላይ የተከፈለ ሲሆን
2.ለአማካሪ መሐንዲሱ ደግሞ ብር 137‚000 እስከ አሁን ድረስ ተከፍሏል፡፡
3.ሕንፃው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከብር 72‚000‚000 ሰባ ሁለት ሚሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡
የሕንፃው አጠቃላይ ይዘትም
1.ሕንፃው ያረፈበት ጠቅላላ ስፋት 580 ሜ.ካሬ ሲሆን
2.የወለሉ ብዛት ከምድር ቤት በታች ፣ ምድር ቤትና ሦስት ፎቅ እንዲሁም ለእስቶር አገልግሎት የሚሰጥ 120 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ነው፡፡
የሕንፃው አገልግሎት
1.ከምድር ቤቱ በታች እስከ አንደኛው ፎቅ ያለው ለመካነ መቃብር አገልግሎት የሚውል፣
2.ሁለተኛው ወለል ደግሞ ለካህናት ማረፊያ የሚውል 21 ክፍሎች፣ 1 የጋራ ማብሰያና ደረጃውን የጠበቀ ሻወርና መጸዳጃ ክፍል የያዘ፣
3.የመጨረሻውና (ሦስተኛው) ፎቅ 476 ሜትር ካሬ ስፋት ያለው ዘመናዊ ሁለገብ አዳራሽ ነው፡፡
4.ከሕንፃው ግራና ቀኝ በ100 ካ.ሜትር ላይ ለአፅም ማሳረፊያ እንዲሆኑ ታስበው የተሠሩ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡
5.ጠቅላላ የፉካዎቹ ብዛት 1396 ሲሆኑ ለአፅም ማሳረፊያ የተዘጋጁት ደግሞ 1205 ፉካዎች ናቸው፡፡
የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ ይህንን ሁለገብ ሕንፃ ለመሥራት ከተነሳባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች፡-
1.ካቴድራሉ በመካነ መቃብር እየተጣበበ መሆኑ ስላሳሰሰበው እና የካቴድራሉንም ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን፣ ውበቱንና ፅዳቱን ከመጠበቅ አንፃር እንዲሁም የምዕመናኑንም የቀብር ቦታ ችግር ለመፍታት፣
2.ካቴድራሉን በኢኮኖሚውም በኩል ራሱን ለማስቻልና የገቢ ምንጭ ለመፍጠር፣
3. በሌላም በኩል የካቴድራሉ አገልጋይ ካህናት ማረፊያ ቤቶች በተበታተነ መልኩ የሚገኙና ከካቴድራሉ አንፃር ሲታዩ አሁን ያሉት የካህናት ማረፊያ ቤቶቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው ችግሩን በከፊልም ቢሆን ለመቅረፍ፣
4.የአዳራሽ ጥያቄ ችግርን ለመፍታት ታስቦ ሲሆን በአነስተኛ ቦታ ላይ ወቅቱን ባማከለ መልኩ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ የልማት ሥራዎች እንዲዘጋጁ በማሰብ ነው፡፡
በሌላም በኩል በኵረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ ለካቴድራሉ በለገሱት ቦታ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ እንደገና በማስቀጠል የሀገሪቱን ብሔራዊ የጨረታ ሕግ ተከትለን በተለያዩ ማስሚዲያዎች ግልጽ ጨረታ በማውጣትና በማወዳደር ጨረታውን ካሸነፈው ባማኮን ኢንጅነሪንግ ከተባለው ሥራ ተቋራጭ ጋር ህጋዊ የኮንስትራክሽን ውል ስምምነት በመፈጸም ቅድመ ክፍያ ብር 4‚152‚000.00 (አራት ሚሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ሁለት ሺህ ብር) ለተቋራጩ በመክፈል በአሁኑ ሰዓት የግንባታ ሥራው ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በቀጣይም የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ ሊያሰራቸው/ሊያከናውናቸው ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል፡-
1ኛ.የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ ዋናውና ግንባር ቀደም ዕቅዱ አድርጎ የሚገኘው የካቴድራሉን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በተገቢው ሁኔታ እንዲታደስ ማድረግ ነው፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር በነቢዩ ሐጌ አድሮ እንደተናገረው “በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳቸሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ሐጌ 1፥4 እንደተባለው ደረጃውን እና የስነ ሕንፃውን እስትራክቸራል ይዘት በጠበቀ መልኩ የካቴድራሉን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዕድሳት አስመልክቶ በእጅጉ የሚያሳስበን ትልቅ ጉዳይ ያለ በመሆኑ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ ሕዝበ ክርስቲያኑ ድረስ እንዲሁም መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትንም ጨምሮ በገንዘብ፣ በሙያ፣ በሐሳብና በሌሎችም ድጋፋችሁና ትብብራችሁ እንዳይለየን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ጥሪያችንን አበክረን እናስተላልፋለን፡፡
2ኛ.የካቴድራሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ግንባታ ሥራ ሲሆን ይህ ት/ቤትም ከዘመን ብዛት የተነሳ ያሉት ክፍሎች እየፈራረሱ ያሉና በእጅጉ የተጎዱ በመሆናቸው ደረጃውን በጠበቀ አዲስ ሕንፃ መተካት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንኑ ሥራ በሁለተኛ ደረጃ ዕቅድ ይዞ ይገኛል፡፡
3ኛ. በካቴድራሉ እና በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ቅፅረ ግቢ የሚገኙትን የመቃብር ቦታዎች በማስተካከል እና አካባቢውን ጽዱ ለማድረግ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ ሂደቱን በማጥናት በቀጣይ የሚነሱ መቃብራትን በማንሳት በዚሁ አዲስ ሕንፃ ሥር በተዘጋጁት የአፅም ማሳረፊያ ፉካዎች ውስጥ ለማሳረፍና የግቢውንም ውበት ጽዳት ለመጠበቅ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታችሁ ሁሉ ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉልን በአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን
{flike}{plusone}