ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተገኝተው የጸሎተ ሐሙስን በዓል አከበሩ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ተክለሃይማኖት ሐሙስ ሚያዝያ 20 ቀን 2008 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመገኘት በካቴድራሉ ለተገኘው በርካታ ምዕመናን አባታዊ ትምህርት እና ቃለ ምዕዳን አስተላልፈዋል፡፡
በአስተላለፉት አባታዊ ትምህርት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ሥርዓተ ትህትናን ማስተማሩንና በማግስቱ አርብ ስለ ሰዎች ሲል ስለሚቆረሰው ሥጋውና ስለሚፈሰው ደሙ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በማያያዝም ቅዱስነታቸው የሥርዓተ ህፅበተ እግር ሥርዓትን መርተዋል፡፡ ከሥርዓተ እፅበተ እግር በፊት በዳዊት መዝሙር የተጻፈው ቃል በዲያቆኑ በዜማ ቀርቧል፡፡ በዲያቆኑ የቀረበው የዳዊት መዝሙር እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡ ትነዝሀኒ በአዛብ ወእነፅህ፤ ተሀጽበኒ እምበረድ ወእጸአዱ፣ ታሰምአኒ ትፍስህተ ወሀሴተ፣ በሄሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፤ ሀሴትንና ደስታን አሰማኝ፡፡ (መዝ. 50÷8) ከዳዊት መዝሙር በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚከተለውን የወንጌል ቃል በንባብ አሰምተዋል፡፡
ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው፡፡ እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ ኢየሱስ አባቱ ሁሉን በእጁ እንደሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደወጣ ወደ እግዚአብሔርም አንዲሄድ አውቆ ከእራት ተነሣ፣ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፣ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፣ የደቀ መዛሙቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ፣ ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ እርሱም ጌታ ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም በኋላ ግን ታስተውለዋህ አለው፡፡ ጴጥሮስም የእኔን እግር ለዘለዓለም አታጥብም አለው፡፡ ኢየሱስም ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ ሆይ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው፡፡ ኢየሱስም የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው፡፡ አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና ስለዚህ ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለ፡፡
እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፡፡ (ዮሐ. 13÷1-19) በማለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን የትህትና ትምህርት ቅዱስነታቸው ለምዕመናን ካሰሙ በኋላ ለሥርዓተ ዕጽበተ እግር የተዘጋጀውን ሂሶጵ (ቅጠል) ባርከው እንደጨረሱ ወገባቸውን ታጥቀው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር እንዳጠበ ሁሉ ቅዱስነታቸውም የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እግር አጥበዋል፡፡
ምንጭ፡-www.addisababa.eotc.org.et
{flike}{plusone}