የጸሎተ ሐሙስ ሕጽበተ እግር ሥርዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከናወነ

0296

በኢትዮጵያ አርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀመረ ዲሜጥሮስ አቆጣጠር መሠረት በየዓመቱ ሲከበር የቆየው የጸሎተ ሐሙስ ሕጽበተ እግር በዓል በዘንድሮውም ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ፓትርያርክ ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ቀሳውስትና ዲያቆናት በየክፍለ ሰዓቱ የተመደበውን ጸሎተ ግብረ ሕማማት በዜማና በንባብ፣ በግእዝና በአማርኛ ቋንቋ አስምተዋል፤ የካቴድራሉ ሊቃውንትም በዓሉን አስመልክቶ በቅዱስ ያሬድ የተደረሰውን ቃል እግዚአብሔር በየክፍለ ጊዜያቱ በዜማ አቅረበዋል ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከጧቱ ሦስት ሰዓት ጀምረው በካቴድራሉ በመገኘት አባታዊ ትምህርትና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር እንዳጠበ ቅዱስነታቸውም የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን እግር አጥበዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በዚያው በካቴድራሉ ለተሰበሰቡ የተለያዩ ተቋማት የሚድያ ባለሙያዎች በዓሉን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፤ቅድስነታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቆሙት በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ለሚኖሩ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች   በዓሉ የሰላም በዓል እንዲሆንላቸውና የተቸገሩትን በመርዳት በዓሉን እንዲያከብሩ አሳስበዋል ፡፡
በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ኃላፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል ፤ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት ትምህርት በዓሉ የአዲስ ኪዳን ሥርዓት የተጀመረበት ፣ቅዱስ ቁርባን ለሐዋርያት የተሰጠበት፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተማሪዎቹን እግር በማጠብ ትህትናን በተግባር ያሳየበት ነው ፤እኛም ከእርሱ ትህትና ልንማር ይገባል ብለዋል ፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖል፡፡

{flike}{plusone}