የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ወቅታዊ አቋም አወጣ

From Photo File

ሰንበት ትምህርት ቤቱ በመግለጫው አሁን ያለበትን ሁኔታ በዝርዝር ያተተ ሲሆን የካቴድራሉ ጽ/ቤት ከብዙ ምክክር እና ውይይት በኋላ በወሰደው የማስተካከያ እርምጃ በጊዜያዊ አመራር እየተመራ ያለ መሆኑ ተገልጿል። ጊዜያዊ አመራሩም ሆነ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላቱ ይህን አቋም ለምን ማውጣት እንዳስፈለገ ሲገልፁ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተናፈሱ ያሉ ወሬወች የሰንበት ትምህርት ቤትቱን ምልአተ ጉባዔ ያላማከለ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቱን ወቅታዊ እና ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ የማይወክል፣ የሰንበት ትምሀርት ቤቱን መገለጫ ባሕርያት እና እሴቶች ማዕከል ያላደረገ በመሆኑ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ በማስፈለጉ መሆኑ ታውቋል። በመሆኑም ማንኛውም በቤተክርስቲያንናችን ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ የሚፈልግ ሁሉ ይህን የጋራ አቋም በማንበብ እውነታውን በመረዳት ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም ማንኛውንም ጥያቄ በሰንበት ትምህርት ቤቱ ጊዜያዊ አመራር በኩል ማቅረብ እና እውነተኛ እና ሚዛናዊ መረጃ በማስተላለፍ በሰንበት ትምህርት ቤታችን አንድነታዊ አገልግሎት እና በቤታችን ሰላም መስፈን ላይ አወንታዊ አሸራችሁን እንድታስቀምጡ በቅድስት ሥላሴ ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል።

ሙሉ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አመራር  መግለጫ እንደሚከለተው ይቀርባል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት በሰንበት ትምህርት ቤታችን ውስጥ የተከሰቱ ችግሮች እና መፍትሔወቻቸው ላይ በተደረገ ውይይት የተያዘ የጋራ አቋም

ቀን፡ 15/06/2011 ዓ.ም

ቦታ፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ጽ/ቤት

አዲስ አበባ

መግቢያ

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ታሪክ ቀዳማዊውን ሥፍራ የሚይዝ ሰንበት ት/ቤት ሲሆን ለዘመናት በምልዓተ ጉባኤው እየተመረጡ በአመራርነት ባገለገሉ ወንድሞችና እህቶች አሁን ካለበት ደረጃ መድረሱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ 2010 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በምልዓተ ጉባኤ የሰንበት ት/ቤቱን አገልግሎት እንዲያስተባብሩ አዲስ ለተመረጡ ሥራ አመራር አባላት ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ለዘመናት የሰንበት ትምህርት ቤቱ መገለጫ የሆኑትን እሴቶች ባልታወቁ ምክንያቶች በመሸርሸር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የነበረን የአገልግሎት ግንኙነት መስመሩን ስቶ እና ተጠሪነታችን ለሰበካ  ጉባኤ መሆኑ እየታወቀ የቤተ ክርስቲያናቸንን የአስተዳደር እርከን ያለፉ ምልልሶች እየተደረጉ መሆናቸውን እንዲሁም ምልአተ ጉባኤው በማያውቀው መንገድ የተሳሳቱ አካሄዶች በተመረጡ አመራሮች እየተፈጸሙ መሆናቸው ስለታወቀ የማስተካከያ ውይይቶች ተደርገው የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ቢወሰንም ውሳኔውን አመራሩ መቀበል ባለመቻሉ እና ከተደጋጋሚ ስህተቱ ሊታረም ባለመቻሉ ሰንበት ትምህርት ቤታችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ተጋርጦ ይገኛል፡፡

የዚህ ስምምነት ዓላማ

ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በአጠቃላይ በሰንበት ትምህርት ቤቱ ህልውና ላይ የተጋረጠበትን ችግር ለመቅረፍ ሲሆን፡-

  1. በአጠቃላይ በሰንበት ትምህርት ቤታችን እና በካቴድራሉ አስተዳደር መካከል ግጭት ተፈጠረ ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ በአካሄድ ስሕተት የተፈጠረ ግለሰባዊ ግጭት እንጂ ሰንበት ትምህርት ቤታችንን የማይወክል መሆኑን ለማብራራት፣
  2.  ከግጭቱ በኋላ በአንዳንድ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት  እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች ፣ አስተያየቶች ፣ የሚዘጋጁ ባነሮች እንዲሁም በማኅበራዊ ድኅረ ገጾች የሚለጠፉ ፎቶግራፎች እና መልዕክቶች ሰንበት ትምህርት ቤቱን እንደማይወክል ለመግለጽ፣
  3.  በሰበካ ጉባኤው የታገዱ አመራሮች በአልታዘዝ ባይነታቸው ከቀጠሉ ሊወስድባቸው ስለሚገባ  እርምጃ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ናቸው፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤታችን መገለጫ ባሕርያት

  1. በትምህርትና በጸሎት ችግሮች እንደሚፈቱ የሚያምን ፣ በታሪካዊ ሂደት ችግሮችን የመፍታት እና የመቋቋም አቅሙን ያዳበረ ፣ ትህትናን እና ታጋሽነትን ገንዘብ ያደረጉ አባላት የሚያገለግሉበት ቀዳማዊ እና አርአያ የሆነ ሰንበት ትምህርት ቤት ነው፣
  2. ሰንበት ትምህርት ቤታችን ሚናውን ለይቶ የሚያውቅ እና የቤተክርስቲያንን አስተዳዳራዊ እርከን ጠብቆ የሚመራ እና የሚታዘዝ እንዲሁም ለምክረ አበው ቅድሚያ የሚሠጥ
  3. ተጠሪነቱ ለሰበካ ጉባኤ መሆኑን ጠንቅቆ የሚያውቅ እና በቃለ አዋዲው የሚመራ፣
  4. በውስጥና በውጭ ግንኙነት ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን የሚከተል፣
  5. ከማኅበረ ካህናቱ ሠላማዊና ፍጹም ጤናማ ግንኙነት ያለው፣
  6. የቤተክርስቲያን አባቶችን፣ታላላቅ ወንድሞችንና እህቶችን የሚያከብር
  7. መንፈሳዊ አገልግሎቱን በትጋት እና በማስተዋል የሚፈጽም፣
  8. የካቴድራሉን የልማት ሥራዎች በሙያ የሚያግዝ ሰንበት ትምህርት ቤት ነው፡፡

ምልአተ ጉባኤው ተስፋ በጣለባቸው ግን እንደተጠበቀው ሆነው ባልተገኙ አመራሮች የተፈጸሙ እና ያልታረሙ  የስህተት እርምጃዎች፡-

ከላይ የተገለጹትን የሰንበት ትምህርት ቤታችን መገለጫ ባሕርያት እና ነባር እሴቶች አስጠብቀው አባላቱን በተሻለ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያሰማሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው የሥራ አመራሮች እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ በራሳቸው የተለየ አቋም ከምልአተ ጉባኤው ይሁንታ ውጭ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡ ይህንንም ያልተገባ አካሄድ ያስተዋሉ ታላላቅ ወንድሞችና እህቶች ቀርበው እንዲያስተካክሉ በተደጋጋሚ ቢመክሯቸውም በአቋማቸው በመጽናት ችግሮችን በመንፈሳዊ መንገድ እንዲፈቱ ከማድረግ ይልቅ በተቃራኒው በመንቀሳቀሳቸው የሰንበት ት/ቤቱን አባላት ለሁለት እንዲከፈሉ ምክንያት ከመሆናቸውም በላይ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡

  1. መረጃ በሌለው እና ቃለ ዓዋዲው በማያዘው ሁኔታ የካቴድራሉ የአስተዳደር ክፍሎችን በሐሰት መክሰስና ግብረ ክህነትን እና የእዝ ሰንሰለትን መጣስ
  2.  ሰንበት ትምህርት ቤቱን ሳያማክሩ እና የምልአተ ጉባኤ ይሁንታ ሳይኖር ጥቂት በጉዳዩ ግንዛቤ  የሌላቸው አባላትን በማስተባበር የሰንበት ትምህርት ቤቱን ዩኒፎርም ለብሰው ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ መሄዳቸው ትክክል እንዳልሆነ ተመክረውም አለመመላሳቸው እና በእምቢተኝነታቸው መቀጠላቸው፣
  3. ሰንበት ትምህርት ቤቱ በቃለ ዓዋዲው ከተሰጠው ድርሻ ውጭ ፣ ባልተረጋገጠ እና በሚመለከታቸው አካላት ማለትም በሰንበት ት/ቤት ማደራጃ መምሪያው ፣ በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ፣ የሰንበት ት/ቤት አንድነት ፣ በሀገረ ስብከቱ አጣሪ ምልልስ እየተካሔደ ባለ  ጉዳይ ላይ በሰንበት ትምህርት ቤቱ ስም እና በግለሰቦች የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ያልተገባ መልእክት በመለጠፍ ምዕመናን የተሳሳተ መረጃ እንዲኖራቸው እና በካቴድራሉ አገልግሎት እንዲጠራጠሩ ማድረጋቸው፣
  4. የሰንበት ት/ቤቱ አባላትን በመከፋፈል የተሳሳተ አቅጣጫ እንዲይዙ ማድረጋቸውና በሰንበት ትምህርት ቤቱ ስም መቀስቀሳቸው፣
  5. በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቱን ቁልፍ እና ንብረት ለጊዜአዊ አመራሩ እንዲያስረክቡ በደብዳቤ ቢታዘዙም ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣
  6.  በጊዜያዊ አመራሩ በኩል በተዳጋጋሚ በወንድማዊ ስሜት ለውይይት ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሊሆኑ አለመቻላቸው እንዲሁም በነባር እና መካር የሆኑ ቀደምት የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ላይ ያልተገባ ስም መስጠታቸው፣
  7. ለሰንበት ት/ቤታችን የወደፊት ተስፋ በሆኑ ታዳጊ ሕጻናት ላይ እየተሠራ ያለው አላስፈላጊ ቅስቀሳ እና ስብሰባ እያደረጉ መሆናቸው፣
  8. ከዚህ ቀደም ማስረጃ የሌላቸው እና ሰንበት ትምህርት ቤቱን የማይመለከቱ ጉዳዮች  በሰንበት ት/ቤቱ ስም እንዳይነሱ ቢነገርም አሁንም አቅጣጫቸውን እየቀያየሩ በተለያዩ መንገዶች የሰንበት ትምህርት ቤቱን ስም በሚያጎድፍ መልኩ ቅስቀሳ እየተካሄደባቸው ያሉ መሆናቸው፣
  9. በሐራ ዘተዋሕዶ ድኅረ ገጽ ላይ ሰንበት ትምህርት ቤቱን ወክለናል በማለት በጥቂት ግለሰቦች የተቀናበሩ እና ምንም ማስረጃ የሌላቸው እንዲሁም ከሰንበት ትምህርት ቤቱ ፍላጎት እና ከቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የሆኑ መንፈሳዊ ሚዛናቸውን የለቀቁ መልእክቶችን ማስተላለፋቸው፣
  10. በተደጋጋሚ በተካሄዱ ውይይቶች ጥፋታቸውን በማመን ይቅርታ ቢጠይቁም ከይቅርታ በኋላ ከጥፋታቸው ሊመለሱ አለመቻላቸው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ቢፈጠሩም የሰንበት ትምህርት ቤቱን አንድነት ፣ ክብር እና የቤተክርስቲያንን ልእልና ለማስጠበቅ ብሎም ከመረጡት ዘመኑን ያልዋጀ እና የተሳሳተ አካሄድ ከነገ ዛሬ ይመለሳሉ በሚል ተስፋ በብዙ ትእግስት ብንመክር ፣ ብናስመክር ሊመለሱ ሲገባ በጥፋታቸው ከእለት እለት ሰንበት ትምህርት ቤቱን በሚጎዳ መልኩ በመቀጠላቸው ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ እርምጃዎችን ወስደናል፡፡

እስካሁን በእኛ በኩል ችግሩን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሔ  እርምጃዎች

  1. በይቅርታ ይመለሱ ዘንድ በምልአተ ጉባኤ ፣ በሥራ አመራር ደረጃ እንዲሁም በታላላቅ ወንድሞች እና እህቶች ተመክረዋል፣
  2. ምንም እንኳ ለመወያየት ፈቃደኛ ባይሆኑም የካቴድራሉ ለጊዜው ከሰየማቸው ጊዜያዊ አመራሮች ጋር ውይይት እንዲካሄድ በተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጓል፣
  3. ከሰንበት ትምህርት ቤቱ አካሄድ ባፈነገጠ መልኩ ከካቴድራሉ አካላት ጋር አሉታዊ ግንኙነት በመፍጠር የሰንበት ትምህርት ቤቱን ባሕርይ የማይወክሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸውን እንዲያቆሙ ተመክረዋል፣
  4. በሰበካ ጉባኤው የእግድ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ በሰንበት ትምህርት ቤቱ አጀንዳ  ብቻ ተመስርተው ማንኛውንም ጥያቄ በአባልነት መንፈስ መስመሩን ተከትለው መጠየቅ የሚችሉ ቢሆንም ሰንበት ትምህርት ቤቱን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ግን ጊዜያዊ አመራሩ እንዲያከናውን በተደጋጋሚ መልእክት ተላልፏል፡፡

የውሳኔ ሃሳብ

ከላይ የጠቀስናቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ቢወሰዱ እና ብዙ ጥረት ቢደረግም ጥቂት ወንድሞች ስሕተታቸውን ተቀብለው ራሳቸውን በምክረ አበው በመገንባት መስተካከል ሲገባቸው ከቀን ቀን የችግር ፈጣሪነታቸው ጉዳይ እየባሰባቸው በመሄዱ የሚከተሉትን ውሳኔዎች በጊዜያዊ የሥራ አመራሩ እና በሰንበት ት/ቤቱ አባላት አንድነት የወሰንን መሆኑን እየገለጽን፡-  

  1. በሐራ ተዋሕዶ ድኅረ ገጽ የቀረበው እውነተኛ ያልሆነ ክስ ማለትም
  2. “በሰላማዊነቱ የሚታወቀውና 75 ዓመት ያስቆጠረው የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት፣ አባ ገብረ ዋሕድ ከተመደቡበት መስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ፥ የልማት ዕንቅፋት፣ ሁከተኛ፣ ስም አጥፊ፣ ፀረ ሰላምና አድማ ቀስቃሽ ተደርጎ ተፈርጇል፤  የሚለው ሃሳብ ካለው እውነታ ጋር የማይገናኝ ሃሳብ ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ባደረግናቸው ስብሰባዎች እና ውይይቶች ክቡር ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ገብረ ዋሕድ በሚያስተላልፉት መልእክት ሁሉ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰላማዊ እና ጥሩ ባሕሪ ያላቸው አባላት ያሉት  ሰንበት ትምህርት ቤት እንደሆነ ሲመሰክሩ የነበሩ አባት ናቸው፡፡ ነገር ግን በሰበካ ጉባኤ የተወከሉት እና ሰንበት ትምህርት ቤቱን  የሚመሩት ወንድም የተወሰኑ አባላትን በማስተባበር ግጭት እንዲፈጠር እና እንዲስፋፋ እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ግለሰባዊ እንጂ የሰንበት ትምህርት ቤቱ እንዳልሆነ አውቃለሁ እያሉ ደጋግመው መስክረዋል፡፡ በመሆኑም ሰንበት ት/ቤታችን በማንኛውም አካል በዚህ መልኩ የተፈረጀ አለመሆኑን እንገልጻለን፡፡
  3. “ከመንፈቅ በላይ የተለፋበት የ75ኛ ዓመት በዓል በአግባቡ እንዳይከበር አበላሹት፣” የሚለውን በተመለከተ የ75ኛ ዓመት በዓል በአግባቡ እንዳይከበር እና ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ እስከ ካቴድራሉ ድረስ የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን እንዳያከናውን ያደረገው የታገደው አመራር በዚህ ባልተገባ እና ለሰንበት ትምህርቱ አንድም ፋይዳ በሌለው ሥራ ወይም ግርግር በመጠመዱ እንጂ ተጠይቆ ያልተመለሰ ፣ ቀርቦ ያልተወሰነ ጉዳይ እንደሌለ እንዲታወቅ፣
  4. “የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ተረኛ እንደ መኾኑ ውል ተይዞ 73ሺሕ ብር ቀብድ የተከፈለበት ጥንግ ድርብ እንዳይደርስና ደረጃውን ባልጠበቀ አለባበስ እንዲያሳልፍ በአስተዳዳሪው ተንኮል ተፈጸመበት፤” የሚለውም በክቡር ሊቀስልጣናቱ ሳይሆን በእኛ ተወካዮች እና በታገደው አመራር በኩል ጥንግ ድርቡን እንዲሰራ በቀረበው ባለሙያ ችግር እንዳልደረሰ አባላቱ ግንዛቤ እንዳለን እንዲታወቅልን፣
  5. “በሰበካ ጉባኤው የተፈቀደለት በጀት በአስተዳዳሪውና በሒሳብ ሹሟ ተቆረጠበት፣” የሚለውን በተመለከተ በሰበካ ጉባኤው ተፈቀደ ማለት በክቡር አስተዳዳሪው ሰብሳቢነት ተፈቀደ ማለት ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ የሥራ እቅድ እያቀረበ እና የአፈጻጸም ሪፖርት እያቀረበ አስፈላጊውን በጀት ይጠይቃል፡፡ ሆኖም በጀት ሲጠየቅ ወጪ በማድረግ በኩል በአስተዳደሩ የአፈፃጸም ክፍተት እንደነበረ ቢታመንም ባደረግነው ውይይት ሕጉን ጠብቆ ለሚቀርብ የፋይናንስ ጥያቄ ካቴድራሉ በተደጋጋሚ በሰጠን አዎንታዊ ምላሽ መሠረት እንደሚፈጸምልን ቃል ተገብቷል፡፡     
  6. “አመራሩ ያለተጨባጭ የእምነትና የሥነ ምግባር ችግር ታግዷል፣” የሚለውም እገዳው የተፈጸመው ከብዙ የምክር አገልግሎት፣ የእርቅ ሙከራ እና ክትትል በኃላ አለመስተካከላቸውን እና እንቅስቃሴቸው እያስከተለ ያለውን አደጋ በተጨባጭ መረጃ ከተያዘ በኋላ እንደሆነ መገንዘባችን እንዲታወቅልን፣
  7. “አባላቱን የመከፋፈል በደል በአስተዳዳሪው ተፈጸመበት” የሚለውም አባላቱ አንድነቱን የማስጠበቅ አደጋ የተጋረጠበት በአስተዳዳሪው ችግር ሳይሆን በታገደው አመራር አልሰማ ባይነት እና አግባብነት የሌለው እና ከሰንበት ት/ቤቱ ውጭ በሚካሄዱ ስብሰባዎች መሆኑ ለማንኛውም ሰው ግልጽ እንዲሆን
  8. በሰበካ ጉባኤው በደብዳቤ የታገዱ አባላት የሚያደርጉት ማናቸውም እንቅስቃሴ እና በማንኛውም ቦታ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሃሳብ አስመስለው የሚጠይቁት ጥያቄ ሰንበት ትምህርት ቤቱን የማይወክል መሆኑ እንዲታወቅልን፣
  9. የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መመሪያው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መመለስ የአንድ ክርስቲያን መገለጫው ነውና በንስሐ እና በምክረ ካህን ከተመለሱና ከተጸጸቱ እንደማንኛውም አባል በሰንበት ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን ማንኛውም አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ መሆኑ እንዲታወቅልን፣
  10. በተደረገው የማጣራት ሂደት ውስጥ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መመሪያውም ሆነ በሀገረ ስብከቱ አጣሪ ቡድን እንደተገለጸው እና ሁላችንም እንደምንረዳው በግለሰቦች የተፈጠረን ግጭት ከሰንበት ትምህርት ቤቱ ተቋማዊ ህልውና ለይቶ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም የካቴድራሉ የአስተዳደር ሠራተኞችም ሆኑ አገልጋይ ካህናቱ ዘንድ ያለው ብዥታ ተቀርፎ በተለመደው መተባበርን እና መከባበርን መሰረት ያደረገ ግንኙነታችን እንድናጠናክር እንዲሁም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤቱ በኩል ይደረግ የነበረው የሰንበት ት/ቤታችን የመልካምነት ምስክርነት እና አስተዳደራዊ ትብብር ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥልልን እንጠይቃለን፣
  11. በተፈጠረው ግርግር እና በተሰራጨው ተገቢ ያልሆኑ መልዕክቶች በአቻ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ ዓለማት ያሉ አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን ዘንድ ከባድ ችግር እንደተፈጠረ፣ ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከካቴድራሉ አስተዳደር ጋር ትልቅ  አታካራ ውስጥ እንደገባ ተደርጎ ስለታሰበ ይህ የሐሰት ወሬ እንደሆነ በካቴድራላችን ዌብሳይት እንዲገለጽልን፣ 
  12. በመጨረሻም የካቴድራሉ ጽ/ቤት ከዚህ ቀደም በታገዱ አመራሮች በኩል ካቴድራሉ ከፍተኛ ምዝበራ ላይ እንደሆነ ያለማስረጃ በደብዳቤ በቀጥታም ይሁን በግልባጭ ለተገለጸላቸው አካላት ሁሉ ለዚህ ጉዳይ ሰንበት ት/ቤቱ እውቅና የሌለው መሆኑ ተገልጾ በደብዳቤ እንዲያሳውቅልን እንጠይቃለን፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለ መስቀሉ ክቡር