ቃለ ዓዋዲው ስለሰንበት ትምህርት ቤት አደረጃጀት ምን ይላል?

መግቢያ

በ2009 ዓ/ም ለ4ኛ ጌዜ ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ ቃለ ዓዋዲ

ሰንበት ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጉብዝናቸው ወራት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ የተጻፈላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የሚያምኑ እና የሚታመኑ ወጣቶች በጉብዝናቸው ወራት ፈጣሪያቸውን ያስቡ ዘንድ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ተጠሪነቱ ለሰበካ ጉባኤው ሆኖ የተደራጀ የወጣቶች የትምህርት፣ የጥናትና ምርምር እና የጸሎት ማዕከል ነው፡፡

ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ስለ ቤተክርስቲያን አደረጃጀት እና መዋቅራዊ አሠራር፣ ስለ ክብረ ክህነት እና ስለ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ሥርዓቶች፣ ስለበጎ ፈቃደኝነት እና ስለ አገልግሎት ዋጋ እንዲሁም ስለ ቃለ-ዓዋዲውም ሆነ ሌሎች ቀኖናዊ መጻሕፍት በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ከተደረገ አገልግሎቱ ስሙር እና ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

አንድ ሰንበት ትምህርት ቤት ከሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትም ሆነ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት ሲያቅድ የቤተክርስቲያናችን መመሪያ የሆነውን እና በቅዱስ ሲኖዶስ ተሻሽሎ የወጣውን እና አሁን በአገልግሎት ላይ ያለውን ቃለ ዓዋዲ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተዘጋጅቶ ለሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተሰራጨውን ሀገራዊ ሕገ ደንብ፣ በአዲሰ አበባ ሀ/ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ያለውን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ (መመሪያ) እና በእንዳንዱ ሰንበት ትምህርት ቤት ያለውን መተዳደሪያ ደንብ መመልከትና የስራ መመሪያ አደርጎ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

ለዛሬ በዚህች አጭር ጽሑፍ ለማሳየት የተሞከረው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ሆኖ እያገለገለ ያለው ቃለ ዓዋዲ ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት አመሠራረት፣ ስለ አስተዳደራዊ ተጠሪነት፣ ስለ አገልግሎት ሚናው  እና ስለ ሌሎች አስተዳደራዊ አካሄዶች ምን ይላል ለሚለው ጥያቄ የሚሆን አጭር ምላሽ መስጠት ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት እና የሥራ ሂደት አፈጻጸም ተመሳሳይነት በቤተ ክርስቲያናችን ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ 

ውድ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ይህን መነሻ ሃሳብ ካነበባችሁ በኋላ በየሰንበት ትምህርት ቤታችሁ ተግባራዊ እንደታደርጉት በመጠቆም ነው፡፡  በተጨማሪም ማንኛውም ጥያቄ ካለ በአካልም ሆነ በጽሑፍ እየጠየቃችሁ የበለጠ እውቀታችንን እንድናሰፋ አደራችን የጠበቀ ነው፡፡

  1. ጥያቄ፡ ሰንበት ትምህርት ቤትን የሚያቋቁምና የሚያደራጅ ማን ነው?

መልስ ሀ፡ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

አንቀጽ 6 ፡ 4. ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተግባር አንዱ የሰንበት ት/ቤትን ማቋቋምና ማጠናከር ነው፡፡

   መልስ ለ፡ ምዕራፍ 4 አንቀጽ 17 ስለ አጥቢያ ቤ/ክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጽ/ቤትና 
                   መቋቋም ያለባቸውን የሥራ ክፍሎች በዝርዝር የሚጠቅስ አንቀጽ ነው፡፡

የአጥቢያ  ሰበካ መንበሳዊ ጉባኤ በቃለ አዋዲው አንቀጽ ° እና ¤ የተገለጸውን አላማና ተግባር ለመፈጸም እንዲችል አንድ ጽ/ቤት እና በሕገ ቤተክርስቲን አንቀጽ ÞÁ ተራ ቁጥር ¢ የተደነገገውንና ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ያቋቁማል፡፡

ሀ) ስብከተ ወንጌል፣                          ቀ) የሒሳብ ክፍል፣

ለ) የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍል፣               በ) የገንዘብ ቤት፣

ሐ) የካህናት አገልግሎት ክፍል፣               ተ) የቁጥጥር ክፍል፣

መ) የሰንበት ት/ቤት ክፍል፣                ቸ) የሕንፃ ሥራ፣ እድሳትና ጥገና ክፍል፣

ሠ) የዕቅድና ልማት ክፍል፣                   ኀ) አኃዛዊ መረጃ /ስታትስቲክስ/ ክፍል፣

ረ) ምግባረ ሠናይ (በጎ አድራጎት ክፍል)፣    ነ) የሰበካ ጉባኤ ማስተባበሪያ ክፍል፣

ሰ) የሕግ ክፍል፣                            ኘ) የገዳማት ክፍል

ሸ) የንዋየ ቅድሳት፣የንብረትና የቅርሳ ቅርስ ክፍል፣

2. ጥያቄ፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ተጠሪነቱ ለማን ነው?

     መልስ፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ተጠሪነቱ ላደራጀው ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ነው፡፡

   አንቀጽ 16፡10. በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተቋቋሙትና የሚቋቋሙት የሥራ ክፍሎች በሙሉ ተጠሪነታቸው ለቤተ  ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት የሰበካ ጉባኤው ሰብሳቢ ወይንም የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ገና ከቅጥራቸው ደብዳቤ ጀምሮ በአሠራር ሂደታቸው ውስጥ በሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ሰንበት ትምህርት ቤቱን ከተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች እንዲጠብቁ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቱን እንዲያደራጁ፣ እንዲከታተሉ እና እንዲቆጣጡሩ መንፈሳዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል ማለት ነው፡፡

3. ጥያቄ፡ ከሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት መካከል ለሰበካ ጉባኤ ተመራጩ ባይኖር እንዴት ይተካል?

መልስ፡ አንቀጽ 11፡ 6. ስለ ተተኪ አባላት ይህን ያስረዳል፡፡

አንድ አባል የሥራ ጊዜው ከማብቃቱ በፊት በሞት ወይም በዝውውር ምክንያት ወይም በአንቀጽ 10 ተራ ቁጥር 2 (ሀ) እስከ (ሐ) የተዘረዘሩትን የማያሟላ መሆኑ ሲታወቅ ወይም ለወረዳው አስተዳደር ጉባኤ በመመረጡ ወይም በሌላ ምክንያት ቦታው ክፍት የሆነ እንደሆነ ባለፈው ምርጫ ከተመረጡት አባላት ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው አባል ሆኖ ቦታውን ይተካል፡፡ በዚህ ዓይነት የሚተካ አባል ከታጣ እንደገና በካህናቱና ምእመናኑ መንፈሳዊ ጉባኤ ድምጽ ብልጫ ተመርጦ የተባለውን ክፍት ቦታ በአባልነት እንዲተካ ይደረጋል፡፡ ተተኪውም አባል የሚያገለግለው የዘመኑ ምርጫ እስኪፈጸም ድረስ ይሆናል፡፡

4. ጥያቄ፡ ሰንበት ትምህርት ቤትን ከማጠናከር አኳያ የአጥቢ ቤ/ክ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ (ሥልጣን እና ኋላፊነት) ምን ይመስላል?

መልስ፡ አንቀጽ 12፡ 5.  የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ከክፉ ነገር ሁሉ የመጠበቅ፣ የሚሰጣቸው  ትምህርትም ሆነ የሚዘምሩት መዝሙር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት መሠረት መሆኑን የማረጋገጥ፣ ሥራቸውና ጠባያቸው ከክርስትያናዊ ሥነ ምግባር ውጭ እንዳይሆን የመከታተል እና የመቆጣጣር ኃላፊነት አለበት፡፡ በሰንበት ት/ቤት ያልተመዘገቡ ወጣቶችን እንዲመዘገቡ፣ በሃይማኖት እና በሥነ ምግባር እንዲጸኑ ያደርጋል ፡፡

5. ጥያቄ፡ ሰንበት ትምህርት ቤትን ከመምራት አንጻር የአጥቢያው ሰበካ ቤ/ክ አስተዳዳሪ ሥልጣን እና ተግባር ምን ይመስላል?

መልስ፡ አንቀጽ 13፡ 4. በአጥቢያው ሰበካ ውስጥ በቃለ ዓቃዲው ምዕራፍ 4 አንቀጽ 16 ተራ ቁጥር 1 የተዘረዘሩትን ንዑሳን ክፍሎች ንዑሳን ክፍሎች እንዲደራጁ እና በትክክል ሥራ ላይ እንዲውሉ ተገቢውንን ክትትል እና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ የልዩ ልዩ ክፍል ሥራ ኃላፊዎችን ያስተባብራል፤ ይቆጣጠራል፡፡

6. ጥያቄ፡ በአጠቃላይ አንድ ሰንበት ትምህርት ቤት  ባደራጀው ሰበካ ጉባኤ ውስጥ ሲንቀሳቀስ መታወቅ ያለባቸው ነጥቦች ምን ምን ናቸው?

መልስ፡ አንቀጽ 21፡1-15. የሰንበት ት/ቤት ክፍል ሥራና ኃላፊነት

ስለ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የሚወጣውን ደንብ እና መመሪያ እየተከታተለ የሰበካው የሰንበት ት/ቤት ክፍል ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

1.  የሰንበት ት/ቤትን በአጥቢያው ሰበካ ቤተ ክርስቲያን ያቋቁማል፣ ያደራጃል፣ በአጥቢያው ሰበካ ከ አራት እስከ ሰላሳ አምስት የእድሜ ክልል የሚገኙት ሕፃናት እና ወጣቶች የሰንት ት/ቤት አባላት ይሆናሉ፡፡ ዲያቆናት በመማር እና ማስተማር በሰንበት ት/ቤቱ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት አባል መሆን የሚችለው ማን ነው?

2.  ለሕፃናት እና ወጣቶች እንደየ ዕድሜያቸው መጠን መምህር በመመደብ በማዕከል ደረጃ በሚወጣው ሥርዓተ ትምህርት መሰረት ትምህርት መሰጠቱን ይከታተላል፡፡

3.  በሰንበት ት/ቤት ውስጥ ተምረው የማስተማር ብቃት ያላቸውን እየመረጠ ተጨማሪ ሥልጠና በመስጠት የበላይ አካልን እያስፈቀደ እንዲያስተምሩ ያደርጋል፡፡ያልተፈቀደላቸው እንዳያስተምሩ ይቆጣጠራል፣ ይከታተላል፡፡

ተተኪ መምህራንን ስለማፍራት

4.  በሰንበት በዐበይት በዓላትና ቀናት የዕለቱን እና የሳምንቱን መርሐ ግብር በማውጣት የቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት፣ የሃይማኖት ትምህርት፣ የቅዳሴ ተሰጥኦ እና የቅዱሳት መፃህፍት ጥናት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡

ስለአገልግሎት እና የሰንበት ትምህርት ቤቱ ድርሻ

5.  ሕፃናትና ወጣቶች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ሃይማት እንዲጸኑ የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት እንዲያውቁና እንዲያከብሩ፣ ግብረ ገብ እንዲሆኑ ከአስተዳደሩ መመሪያ እየተቀበለና በቅርብ እየተከታተለ ያስተምራል፣ ይመክራል፣ ይቆጣጠራል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሥራዎችን የሚያከናውነው ከሰበካ ጉባኤ አስተዳደሩ መመሪያ እተቀበለ ስለመሆኑ

6.  ለምዕማናን ትምህርት የሚሰጡ በሊቃውንት ጉባኤ የተመረመሩ እና በማዕከል የተፈቀዱ መንፈሳዊ መዝሙራትን እንዲያጠኑ የዕለት እና የሳምንት መርሐ ግብር ያዘጋጃል፡፡

7.  ወጣቶች መንፈሳዊ እውቀታቸው እንዲዳብር ልዩ ልዩ የመማሪያ መሣሪያዎች የሚገኙበት ቤተ መፃሕፍት ያቋቁማል፡፡

ቅድመ አገልግሎት ምርመራ እና ሳነሱር እና የሰበካ ጉባኤው ኃላፊነት

8. ከሰንበት ተማሪዎች በበዓላትም ሆነ በሌላ ዝግጅት ግዜ በትርኢት መልክ የሚቀርቡ መንፈሳዊ ዝግጅት በቅድሚያ ለሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ቀርቦ ከተመረመረና ከተጠና በኋላ ሲፈቀድ በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቱ ገቢ አሰባሰብ ሂደት እና አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት

9. የሰንት ት/ቤት ተማሪዎች በማንኛውም መንገድ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰበስቡት ገንዘብ ለአጥቢያው ሰበካ ጉባኤ ገንዘብ ቤት ገቢ ይሆናል፡፡ ለሚያስፈልጋቸው መጪ ዝርዝር ጥናቱ ለሰበካው መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ቀርቦ ሲፈቀድ በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡

10. ማንኛውንም የሚሰበስቡትን ሀብት ገንዘቡት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴል 30 እና 64 ንብረቱን በሞዴል 19 ሰብስቦ ለአጥቢያው  ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ  ጽ/ቤት ገቢ ያስደርጋል፡፡ ገንዘቡን እና ንብረቱንም በአጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያስመረምራል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት አመራር ምርጫ እና የአገልግሎት ጊዜ

11. የሰንበት ት/ቤት አመራር ሊሆኑ የሚገባቸው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶች ሆነው በሰበካ ጉባኤው አስመራጭነት በመላው የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ይመረጣሉ፡፡ የሚያገለግሉትም ለ3 ዓመታት ይሆናል፡፡ የሰንበት ት/ቤት አባላት ከፈለጓቸው ለሁለተኛ ግዜ ብቻ ተመርጠው ለ£ ዓመታት ያገለግላሉ፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤትና የንስሐ አባቶች ግንኙነት

12. ቀሳውስት የንስሐ ልጆቻቸው ልጆች መንፈሳዊውን ትምህርት እንዲከታተሉ ወላጆችም ልጆቻቸው በሰንበት ት/ቤት ተመዝግበው መንፈሳዊውን እውቀት እንዲቀስሙ ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታቸው መሆኑን ያሳውቃል፤ ይከታተላል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ልዩ አልባሳት ሊኖራቸው እንደሚገባ

13. የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች መንፈሳዊውን በዓል በሚያከብሩበት ግዜ የቤተ ክርስቲያናችንን እምነት እና ሥርዓት በተከተለ ሁኔታ የመለያ ልብስ (ዩኒፎርም) እንዲዘጋጅላቸው ያስደርጋል፡፡

14. በሰበካ ጉባኤ ወይም ከዛ በላይ በሆነ አካል ካልታወቀ እን በጽሑፍ ካልተፈቀደ በስተቀር በሰንበት ት/ቤት ስም የአዳር መርሐግብር እንዳይደረግ በጥብቅ ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፡፡

15. ከስብከተ ወንጌል እና መንፈሳዊ ት/ቤት ክፍሎች ጋር በመተባበር በሀገረ ስብከቱ እንዲያስተምሩ የተፈቀደላቸው መምህራንን ብቻ እየጋበዘ ለሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ብቃትና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጣቸው ያስደርጋል፡፡

ማጠቃለያ

ከዚህ በላይ ያየናቸው አንቀጾች በሙሉ ሰንበት ትምህርት ቤትን ብቻ የተመለከቱ ናቸው፡፡ እነዚህን አንቀጾች በሚገባ መረዳት እና ቅንነት በተሞላበት አስተሳሰብ መመልከት ወጥነት ላለው አገልግሎት መሠረት የሚጥል እውነታ ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤትን እና የአካባቢ ወጣቶችን በአገልግሎት ለመድረስ  በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና ለአገልግሎቱም በሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች ውስጥ እነዚህ አንቀጾች ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ማንኛውም ደንብ እና መመሪያ እነዚህን የቃለ ዓዋዲ ሕጎች ተቃርኖ መውጣት አይኖርበትም በስህተት ወጥቶም ከተገኘ ወዲያውኑ የማስተካከያ እርማት ይደረግበታል፡፡

ወስብሀት ለእግዚብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!!!